Sunday, February 15, 2015

ከጦቢያችን ጋራ ዘላለም ይኖራል (kethiopiachin gara zelalem ynoral)

ከጦቢያችን ጋራ ዘላለም ይኖራል (ለሀይሉ (ገሞራው) ገ/ዮሀንስ መታሰቢያ) ኢትዮጵያን ኢትዮጵያን ኢትዮጵያን እንዳለ አሸለበ ሀይሉ ለጊዜው ዝም አለ። ሰላም ዕድገት ፍቅር በጦብያችን ሙሉ፤ ሀገር ወገን ስትል ወንዜ ሸንተረሩ፤ ሁሉም እንደዋዛ አልክሳ ይቅሩ። ስትገጥም ስትቀኝ ስትጽፍ የነበርክ፤ እማዬ ውዲቱ ኢትዮጵያዬ እያልከ፤ ታጠፈ ወይ እጅህ ደከመህ ወይ አሁን፤ እግዜር ያጽናሽ አልካት እናትክን ኢትዮጵያን። ግን ማን አስተማረህ በናት መጨከኑን፤ የወገንን ብሶት አይቶ አላየ መሆን፤ ፀጥ-ረጭ ማለቱን ዝምታ መምረጡን። ግናስ ይበቃሀል ብዙ ወትውተሀል፤ እማዬን ኢትዮጵያን ጠብቁልኝ ስትል፤ እናቴን ኢትዮጵያን አታስነኩ ስትል፤ ጽፈሀል ገጥመሀል ብዙ አስተምረሀል፤ በረከተ-መርገም ብለህ ፈር ቀደሀል፤ ታዲያ! ነፍሴ ትረፍ ብትል የት ላይ አጥፍተሀል? እናም! እረፍት ወሰደ እንጂ ጋሽ ሀይሉ አልሞተም፤ ሲኖርላት ኖሮ አሁን አይረሳትም፤ በፍፁም ኢትዮጵያን ዛሬ አይዘነጋትም። ሁሌም ከውዲቱ ከጦቢያችን ጋር ነው፤ ለኛ አልሞተም ሀይሉ ገሞራው ሀያል ነው። ሀይሉ ግጥም ሆኗል ሲነበብ ይኖራል፤ የሁላችን ድጋፍ ሀይሉ ሀውልት ሆኗል፤ ዘላለም ይኖራል ሀይሉ መንፈስ ሆኗል፤ ከጦቢያችን ጋራ ዘላለም ይኖራል። (ከእንዳለ ከተፎ ዶ/ር - 2014/11/29)

ሀ ሳይሉ ጥፈት ውል ሳይዙ ሙግት (Ha sailu tifet wel saizu muget)

ሀ ሳይሉ ጥፈት ውል ሳይዙ ሙግት አንድ ቀን በOMN YOU TUBE በተዘጋጀ ፕሮግራም በፈቃዱ ሞረዳ ለኣይተ ተስፋይ ገብረዓብ ያደረገለትን ቃለመጠይቅ ተከታትዬ ነበር። በቃለመጠይቁ ያዳመጥኩት ሁለቱንም እንድታዘብ አድርጎኛል፣ ነጭ ውሸት የተደመጠበት ቃለመጠይቅ፣ ይህ በተለይ መልስ ሰጪውን ይመለከታል። በፈቃዱ ጥያቄውን ጀምሮ ጥቂት ከሄዱ በኋላ አንድ ቦታ ላይ ሲደርሱ ኣይተ ተስፋይን፣ “ከአሁን በኋላ ኦሮሞ ነህ ማለት ነው” ብሎ ጠየቀው። የተሰጠው መልስ፣ “በፊትም ኦሮሞ ነበርኩ። በኦሮሞ ሕዝብ መካከል ተወልጄ ያደኩ በመሆኔ በፊትም ኦሮሞ ነኝ። አደአ እትብቴ የተቀበረበት የማንነቴ አካል ነው።” የሚል ነበር። በዚህን ጊዜ እንደ ሳተና ጋዜጠኛ፣ በፈቃዱ የተጠያቂውን ታሪካዊ ድርጊቶች ከሚናገራቸው አነጻጽሮ የሰውዬውን አቋም ለማወቅ ሌሎች ጥያቄዎች ሊያስከትል ይችል ነበር። ግን አላደረገውም፣ በመልሱ የረካ ይመስላል። ታዲያ ሰውዬው ከኦሮሞዎቹ የበለጠ ኦሮሞ መሆኑን መናገር ጀመረ። በኢትዮጵያ ብኄራዊ ውትድርና ተመልምሎ ውጊያ ወረዳ ውስጥ ከተማረከ በኋላ ለማገልገል የመረጠው ሕወሀትን እንጂ ኦሕዴድን ወይም ኦነግን አይደለም። በዚህ ረገድ የሰውዬው ኦሮሞነት የቱላይ ነው? ለኦሮሞ ብኄር ንቅናቄ ከሚታገሉ ድርጅቶች አንዱ ውስጥ እንኳ ተሳትፎ ሳያደርግ በተቃራኒው ለሌላ ብኄራዊ ንቅናቄ የታገለ ሰው ኦሮሞ ነኝ በማለት ለመናገርም ሆነ ለመጻፍ የሞራል ብቃት የለውም፣ ለዚያውም ኦሮሞ ያልሆነ።ሰውዬ የሚያደርገውን ዓይን ያጣ ሽወዳ ህጻን ልጅን እንኳ አያታልልም። ዶ/ር መረራንም ሆነ ዶ/ር ነጋሶን እንኳን መተቸት ይቅርና እነሱ ለኦሮሞ ሕዝብ ስለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቅንጣት ታህል የተዛባ አስተያየት ለማድረግ ሊዳዳው አይገባም፣ ምክንያቱም እነዚህ ሁለት ሰዎች ባመኑበት ዓላማ ለኦሮሞ ኅዝብ ብኄራዊ ንቅናቄ እየሠሩ ነው ያሉት። ተራ ሽንገላ ውስጥ በመግባት ከሚየደርገው የሚናገረው የሚታመንለት ስለመሰለው አድማጭንና አንባቢን በሀሰት ፈረስ ሽምጥ ሌጣውን ሊጋልበው ይመኛል። ስለ ታላቁ የብዕር ሰው ፀጋዬ ገብረመድኅን በዚህ ቃለመጠይቅ ተነስቷል። እዚህ ላይ ኣይተ ተስፋይ የሚነግረን የኦሮሞን ኅዝብ ትግል በጽሑፍ መመለስ እንደሚገባ ታላቁ ደራሲ አርአያ እንደሆነው ነው። ለዚህ እንደማስረጃ የሚሰጠው ፀጋዬ ስለ አዋሽ በጻፈው ግጥም ውስጥ የኦሮምኛ ቃላት መጨመሩን ነው።(አንባቢ ለፍርድ እንዲመቸው ፀጋዬ ስለ አዋሽ የጻፈውን ቢያነብ ጥሩ ይሆናል።) ፀጋዬ የሀሳቡን ጥልቀትና ውበት ለመግልጽ አይደልም ኦሮምኛ ሌሎችንም የኢትይጵያ ቋንቋዎች ቢጠቀም የብኄረተኛ ጎራ ውስጥ መመደቡ ግልብነት ነው። ግዕዝንም ይጠቀም እንደነበር ማስታወስ የግድ ይሏል። በእንግሊዝኛ ሥነጽሑፍ ውስጥ የፈረንሳይኛ ቃላትና ሀረጎች ይግኛሉ፣ ሃሳብንና ውበትን ለመግልጽ ነው። ደራሲ ፀጋዬ ገብረመድኅን እኮ “ጴጥሮስ ያችን ሰዓት”ና “ቴዎድሮስ”ን የጻፈ ደራሲ ነው። እንደነዚህ ያሉት መጽሐፍት ውስጥ ያሉ ጥልቅ የሆኑ ሀገራዊ ጽንሰሃሳቦችን በመደበቅ “አዋሽ” ውስጥ ተሰባጥረው የሚገኙትን ጥቂት የኦሮምኛ ቃላት ብቻ መዞ ፀጋዬን በብኄረኛነት መመድብ የፀጋዬ ሥራ በተንሸዋረረ መነጽር እንደተነበበ ያሳያል፣ አለበለዚያ ደግሞ የግል ዓላማን ለማራመድ በችኮላ ሳይስተዋሉ ከፀጋዬ የተቃረሙ አረፍተ ነገሮች ናቸው። ጴጥሮስ ያችን ሰዓት ውስጥ አቡነ ጴጥሮስና ባንዳው ሹምባሽ ጊርሻ የሚያደርጉትን ንግግር ያነበበ ወይም ያዳመጠ ሀገርን በሚመለከት የጸጋዬን የሀሳብ ምጥቀትና ረቂቅነት ለመገንዘብ ይችላል። ኣይተ ተስፋይ ወይ የፀጋዬን ሥራዎች አላያቸውም አለበለዚያ የሚደብረውን በመግደፍ ወይም ለስሜት ቅኝቱ ተስማሚ የሚሆኑለትን እየነቀሰ ይወስዳል። ፀጋዬ እንኳን ለገራችን ባሕልና ቅርስ ለአፍሪካም የሚቆረቆር ሰው ነበር። የአክሱም ሃውልት ከሮም ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ከታገሉት ታላላቅ አገር ወዳዶች አንዱ ፀጋዬ ነበር። ይህን ሊያይ ባለመቻሉ ኣይተ ተስፋይ የፀጋዬ ገብረመድኅንን ሥራዎች እንደማያውቃቸው አሳይቶናል። ኣይተ ተስፋይ እንደሚለን ሌላው የኦሮሞን ኅዝብ ትግል በጽሑፍ መመለስ እንደሚግባ አርአያ የሆነው ሰው እውቁ ደራሲ በዓሉ ግርማ ነው። በዓሉ ግርማ ኦሮማይን አዘጋጅቶ ለአንባብያን ያቀረበው በዚያን ጊዜ በነበረው በኢትዮጵያ መንግስትና ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ይጥር ከነበረው ከሻእቢያ ጋር የተደረገውን ውስብስብ፣ ረጅምና አስቸጋሪ ትግል ለማሳየት ነው። የመጽሐፉን ተራኪ ያደረገው ጸጋዬ ኃይለማርያም የተባለውን ጋዜጠኛ ነው። ከሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በየጎራቸው የተሰማሩ በርካታ ገጸባሕርያት ይገኛሉ። ሻለቃ ታደሰ ቆርቾ አንዱ ሲሆን ከሻእቢያ በኩል ደግሞ ሰዕላይ ባራኺና ዑቅበ ሲላ(ወዲ ሲላ) ይገኙበታል። ወዲ ሲላ በሜካኒክነት አስመራ አርሚ አቭዬሽን ከሻለቃ ታደሰ ቆርቾ ጋር ይሰራ የነበረ ነው። በሻእቢያ የተተከለ፣ የሻእቢያ ዕቅድ አስፈጻሚ ሰው ነው። ኦሮማይ መጽሐፍን ከሃ እስከ ፐ ፈትሹ። ያለበለዚያ የሻለቃውን ድርጊት የሚያሳዪ በነቂስ መጽሐፉ ውስጥ ያሉትን ከሚከተለው ተመልከቱ፣ ሻለቃ ታደሰ ቆርቾ ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ ከአርሚ አቪዬሽን ሜዳ በውርርድ አይትጣም። ላለፉት ሰባት አመታት ከከፍተኛ ባለስልጣን ጀምሮ እስከ ተራ ሰው ያለው ሁሉ የሚያውቀው የታወቀ ተቋም ሆኖዋል። የአርሚ አቪዬሽን ትራፊክና ስምሪት አዛዥ ነው። በጣም ቁልፍ የሆነ ቦታ ነው የያዘው። ያለ እሱ በጎ ፈቃድና ውሳኔ በአርሚ አቪዬሽን ሄሊኮፕተሮችና አይሮፕላኖች የሚያጓጉዝም ሆነ እቃ የሚጭን ሰው የለም። በእዙ ስር ያሉት አይሮፕላኖች ሁሉ በየትኛው ደቂቃ የት ቦታ ላይ ምን በመስራት ላይ እንዳሉ በቃሉ ያውቃል። (ገጽ 32) ሻለቃ ታደሰ ቆርቾ እንደ ድሮው በፈገግታ አልተቀበለኝም። ሰውነቱ ከሳ ብሉዋል። እንዲያው ሲመለከቱት ስጋት ያለበት ሰው ይመስላል። ስራ በዝቶበት ይሆናል በማለት ቀዝቀዝ ስላለብኝ ቅር አላለኝም። የጦር አይሮፕላኖች፣ ሄሊኮፕተሮች፣ ትናንሽ አይሮፕላኖች በየደቂቃው ይነሳሉ፣ ይወርዳሉ፣ ሰውና ዕቃ ይጫንና ይወርዳል፣ አርሚ አቪዬሽን የእብድ ሰፈር መስሏል። ግን ሻለቃ ታደሰ አይሮፕላኖች ሲነሱና ሲያርፉ ማየት እንደ በፊቱ ደስ የሚለው አይመስልም። እንዲያውም አያያቸውም። በሌሎች ጊዜያት ወታደር ጠርቶ ያስጭን ነበር። ዛሬ ግን ፊልሞቹ የታሸጉበትን ካርቶን ራሱ ይዞ ወደ ተዘጋጀው አይሮፕላን ሲሮጥ በማየቴ ደስ አለኝ። ወደ መኪናዬ ተመለስኩ። የመኪናዬን ሞተር አስነስቼ ልኼድ ስል ኪሴ ውስጥ የዘነጋሁት አንድ ጥቅል ፊልም ትዝ ብሎኝ ሞተሩን አጠፋሁና ተነስቼ ሻለቃ ታደሰን ፍለጋ ሮጥኩ። አገኘሁት። ካንድ ረጅም፣ ቀጭን፣ የሜካኒክ ቱታ ከለበሰ ጠይም ወጣት ጋር ብሹክሹክታ እየተነጋገረ ፊልም ወደ አዲስ አበባ እንድትወስድልን ከተመደበችው ልዩ አይሮፕላን ላይ ዕቃ ይጭን ነበር። የማዳም ሜሎቲ አይሮፕላን የነበረች ናት። ዘወር ባለ ስፍራ ነበር የቆምችው። በሚለዋወጡት የሹክሹክታ ንግግር ተመስጠው ነበር መሰለኝ ከኋላቸው ስመጣ ሁለቱም አላዩኝም፣ አልሰሙኝም። የያዙትን ስራ ያጣድፋሉ። “ጓድ ሻለቃ” ብዬ ጠራሁት። ሻለቃ ታደሰ ድንገት ወደኔ ዞር አለ፣ ለሁለት ይዘውት የነበረው ከባድ ካርቶን ከሁለተኛው ሰው እጅ አምልጦ አስፋልት ላይ ወርዶ ዘጭ ሲል ታሽጎ የነበረው ካርቶን ካንድ ጎን ተበጥርቆ አፉን ከፈተ። አይኖቼ መሬት ከወደቀው ካርቶን ላይ ተተክለው ቀሩ። ገና ከፋብሪካ የወጡ የሚመስሉ አዳዲስ ክላሽን መትረየስ መሳርያዎች ብቅ ብለው ይታዩ ነበር። አላስገረመኝም። ይልቅ እንደ አዲስ ነገር ሆኖ ያስገመረኝ ነገር ቢኖር የሁለቱ ሰዎች ድንጋጤ ነበር። (ገጽ 182፣ 183) “ጊዜው አስቸጋሪ ሆኗል” አለ ተከስተ ከረጅም ዝምታ በኋላ። ወደ ወዲ ሲላ መለስ በማለት፣ “ይህ የአርሚ አቪዬሽን ሰውዬ ስሙ ማነው አልከኝ?” አለው። “ሻለቃ ታደሰ ቆርቾ።” “የሚታመን ሰው ነው?” “ከእንግዲህ ምርጫ የለውም። እኛ ትብብሩን እንፈልጋለን፣ እሱ ገንዘባችንን ይፈልጋል። ጡረታ የመውጫው ጊዜ የደረሰ ሰው ነው። ግን ገንዘብ እየጠየቀ አስቸግሯል” አለው። “የጠየቀውን ክፈሉት፣ ሰውዬው ያስፈልገናል” ። “ዛሬ ጉድ ሆነን ንበር” አለ ወዲ ሲላ። “ምን ሆናችሁ?” አለ ሰዕላይ። “አዲሳባዎች የጠየቁንን መሣርያ ስንጭን ፀጋዬ ጋዜጠኛው ደርሶብን ነበር። ጅሉ ደንግጦ ካርቶኑን ለቀቀው......” “እና!?” አለ ሥዕላይ ቅንድቦቹን ከፍና ዝቅ እያደረገ። “መሣሪያዎቹን አይቷል። ግን የገባው ነገር ያለ አይመስለኝም.......” (ገጽ 222 እና 223) ወጣቱ ሜካኒክ ከኛ ፈንጠር ብሎ ቆሞ ይመለከተን ነበር። “ሻለቃ ፈጠን በል እንጂ” አለው። ሻለቃ ታደሰ የበላይ ባለሥልጣን ያዘዘው ይመስል በካርቶን የታሸጉትን ፊልሞች ራሱ ተሸክሞ ሊሄድ ሲል “ማነው ይህ ሰው?” አልኩት። “ለጥያቄዬ መልስ ሳይሰጠኝ ፣ “የረሳሀው ነገር አለ?” አለኝ። “ካልክስ አለ” አልኩት። “ምን?” ብሎ አፈጠጠብኝ። “ፊልም.....” “የት ነው ያለው!” “መንገድ ላይ። እየጠበኩ ነው። ይቅርታ ትንሽ መጠበቅ ይኖርብናል” አልኩት። ወጣቱ ሜካኒክ ትእግስቱን ጨርሶ ነው መሰለኝ ወደኛ መጣ። “ምንድነው የምንጠብቀው!?” አለ። ሻለቃ ታደሰ ሁኔታውን አስረዳው። ወጣቱ ያደረበትን ብስጭት ለመሸሸግ ቢሞክርም አልሆነለትም። “ጓድ እንተዋወቅ ፀጋዬ ኃይለማርያም እባላለሁ” አልኩት። ትንሽ አመነታና፣ “ዕቁበ ሲላ እባላለሁ” ብሎኝ ፈገግ አለ። “ጥድፊያው ምንድነው? አይሮፕላኗ እንደሆነች ለኛ ሥራ ብቻ ነው የታዘዘችው አይደለም እንዴ?” አልኩት። “ቢሆንም በጊዜ መሄድና መምጣት አለባት.....” “ሜካኒክ ነኽ አይደለህም?” “ነኝ። ምነው?” “በትራፊክ ቁጥጥር ሥራ ታዲያ ምን ያገባሀል? ብዬ ነው” አልኩት። ሻለቃ ታደሰ ያልበው ጀመር። “በማንኛውም ሥራ መተባበር ኃጢአት ነው እንዴ?” ብሎኝ ቀጠለና፣ “አንዱ አይሮፕላን ከመሄዱ በፊት የሌላውን ጥገና ሥራ ለመጀመር አልችልም። እና በዚህ ሰሞን ማንም ጊዜ የለውም” አለኝ። እንደሚያታልለኝ ገባኝ። የሻለቃ ታደሰ ሁኔታ የዕቁባይን ውሸት አጋልጦ ያሳይ ነበር። ምን እንደሚሠሩ ወይም ምን ለማድረግ እንደተዘጋጁ ባላውቅም ቅሉ፣ ከዚህ ቀደም ከእጃቸው አምልጦ የወደቀው መሣርያ መጥቶ ፊቴ ድቅን አለ። የሻለቃ ታደሰ ድንጋጤ ታየኝ። ኮሎኔል በትሩ ተሰማ አስመራ የገባን ለት..... በተለይም ዕድሜው ለጡረታ የደረሰና የገንዘብ ችግር ያለበትን ሰው አሳደው ነው የሚጠቀሙብት ..... ሲል የተናገራቸው ቃላት ከጆሮዬ ላይ ደወሉ። ፍጹም ሊሆን አይችልም! እንዴት ሊሆን ይችላል? ሻለቃ ታደሰን የመሰለ ጀግና ሰው ክብረ ሕሊናውን ለጥቅም አሳልፎ ሊሸጥ አይችልም አልኩ በልቤ። (ገጽ 243፣ 244) በስለላና በግድያ ተግባር ላይ የተሰማሩ በቁጥር ከአምስት መቶ በላይ የሆኑ የሰዎች ስም ዝርዝርና እንዲሁም ለግድያ የሚፈለጉ የሲቪልና ወታደራዊ ባለሥልጣኖችና ኃላፊዎች የሕዝባውያን ድርጅቶች ተወካዮች ስም እንዳለ ተገኘ። የኦሮማይን ተልእኮ በቅጥረኛነት የሚያስፈጽሙ ሰዎች ስም ነበር። ኮሎኔል በትሩ የሻለቃ ታደሰ ቆርቾን ስም ሲያይ ራሱን ይዞ ቀረ። (ገጽ 367) እኔም ስለ ሻለቃው የኦሮሞ ታጋይነት ከኣይተ ተስፋይ ስሰማ ራሴን ይዤ ቀረሁ። ይህ አባአል ሙገሳ ነው ስድብ? በምን ተአምር ነው ሻለቃ ታደሰ በዚህ አድራጎቱ በኦሮሞ ብኄራዊ ንቅናቄ ተሳታፊነቱ ሊፈረጅ የሚችለው? ለሻዕቢያ መሥራት ለኦሮሞነት መሥራት ነው? ተስፋይ ከኦሮማይ መጽሐፍ አንድ ሰንበሌጥ በመምዘዝ፣ ያውም በዓሉ ለሻለቃ ታደሰ ቆርቾ የሰጠው ገፀ-ባሕሪን ሙሉ በሙሉ በሚቃረን መልኩ፣ ታደሰ ቆርቾን ለኦሮሞ ኅዝብ ይታገል እንደነበረ የሚነግረን እንደሚከተለው ነው፣ “ታደሰ ቆርቾ በድብቅ መሣሪያ ሲያመላልስ ይዘረገፍበትና ኃይለማርያም(ፀጋዬ መሆኑን ዘንግቶታል) ያየዋል። ይኼ ደግሞ የኦሮሞ ሰዎች ትግል ላይ እንዳሉ ፍንጭ ይሰጠን ነበር።” መቼስ አይታወቅ አፍ ሲያድጥ፣ እንዲሁም ሲከት ወደ ማጥ። ኣይተ ተስፋይ ብዙ ማሰነ፣ ብዙ ለፋ ውጤቱ ግን ሀሰትን ሸጦ ቅሌትን ማትረፍ ነው። በኦሮማይ መጽሐፍ ውስጥ ሻለቃ ታደሰ ቆርቾ በይፋ የኢትዮጵያ መንግስት ወታደራዊ መኮንን ነው፣ በሕቡእ ደግሞ በገንዘብ በሻእቢያ ተገዝቶ ሃላፊነቱን ለክህደት ያዋለ ሰው ነው።በመጽሐፉ ውስጥ ይኽ ነበር የሻለቃው የሥራ ድርሻ። ሻለቃው ያላደረገውን ገድል ለኦሮሞ ብኄራዊ እንቅስቃሴ ገጸ-በረከት ማቅረብ ተራ ፌዝ ነው። ኣይተ ተስፋይ የለፈፈው ነጭ ውሸት ምንጩ አንዱ መጽሐፉን በደንብ አንብቦ አለመረዳት፣ ሌላው ደግሞ ጫፍ በማስያዝ አድማጭን ወይም አንባቢን ሸውዶ ለማለፍ ነው።በዘመነ ቴክኖሎጂ፣ ሰው ቤቱ ቁጭ ብሎ መረጃ ማግኘት በሚችልበት ጊዜ የባለሙያዎችን ሥራ በጥራዝነጠቅነት ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ ፀረ-መረጃ ሥራ ላይ መሰማራት ነው። ይህን አይቶ በሌሎች ጻፍኳቸው በሚለው ውስጥ ከዚህ ያልተናነሱ አወናባጅና መናኛ ሀሳቦች እንደማይኖሩ የሚያስተማምን ምንም ነገር አይኖርም። ከእሸቱ አሜሪካ